የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ሀገራት የጤና ድንገተኛና ፈጣን ምላሽ ዝግጁነት ኮሚቴ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

By Feven Bishaw

November 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሁለተኛው የአፍሪካ ሀገራት የጤና ድንገተኛና ፈጣን ምላሽ ዝግጁነት ኮሚቴ ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት የጤና ዘርፍ አመራሮችና የተለያዩ የልማት አጋሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባዔ በጤናው ዘርፍ ድንገተኛና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥን አስመልክቶ ስለሚኖሩ ተግባራትና አፈጻጸም ግምገማ የሚካሄድ ሲሆን፤ የጤና ተቋማት ጉብኝትም እንደሚኖር ተመላክቷል።

መድረኩ ሀገራት የአፈጻጸም ሪፖርቶቻቸውን የሚያቀርቡበት፤ ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩበት፣ ከሌሎች ዓለም አቀፍና ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚካሄድበት ተገልጿል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በመድረኩ፤ ጉባኤው በጤናው ዘርፍ ለሚታዩ ችግሮች የጋራ መፍትሄ የምናመላክትበት ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የጤና፣ የድንገተኛና ፈጣን ምላሽ ዝግጁነት ሥራዎች ድንበር ዘለል ትብብሮችን የሚጠይቁ በመሆናቸው በቅንጅት መሥራት የግድ መሆኑን ገልጸው፤ ትበብር ለችግር የማይበገር የጤና ሥርዓት ለመዘርጋት ለሚደረገው ጥረት መሰረት የሚጥል መሆኑን አስገንዝበዋል።

የመጀመሪያው የአፍሪካ ሀገራት የጤና ድንገተኛና ፈጣን ምላሽ ዝግጁነት ኮሚቴ ጉባኤ ባለፈው ዓመት በኬንያ መካሄዱ ይታወሳል።