የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና እንግሊዝ ለቀጣናው ሰላም በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ገለጹ

By amele Demisew

November 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና እንግሊዝ ለቀጣናው ሰላም እና ደኀንነት መረጋገጥ በጋራ መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከእንግሊዝ የአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባሕር ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር አሊሰን ብላክበርን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም አምባሳደር ምስጋኑ÷ የአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታንና ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ያላትን ሚና በተመለከተ ለልዩ መልዕክተኛዋ የገለፁ ሲሆን÷በቀጣናው ለሚስተዋሉ ፈተናዎች መፍትሔ የእንግሊዝ አጋርነትና ትብብርን አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

አምባሳደር አሊሰን ብላክበርን በበኩላቸው÷ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት ኢትዮጵያ እያበረከተችው ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።

እንግሊዝ የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት በትብብር ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነት እና በቀጣናው ባሉ የጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ በቅንጅት ለመሥራት ያላትን ፍላጎት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

በቀጣናው የሚስተዋሉ ፈተናዎችን አጋርነት እና ትብብርን የበለጠ በማጠናከር ለመፍታት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንደሚገባም በውይይቱ ተነስቷል።