አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ከባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ወሎ እና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የሥነ-ምድር ካርታ ሥራና የማዕድን ክምችት ጥናትና ልየታ ለማከናወን ስምምነት ላይ ደርሷል።
ጥናቱ በ5 ሺህ 254 ካሬ ኪ/ሜትር ላይ የሥነ-ምድር ጥናትና ካርታ ሥራ እንዲሁም በ70 ካሬ ኪ/ሜትር ላይ ደግሞ ዝርዝር የማዕድናት ስርጭት፣ ክምችትና ጥራትን መለየት ያስችላል ተብሏል።
የማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊው አቶ ኃይሌ አበራ እንደገለጹት፥ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ለማዕድን ሃብት ልማት ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ በክልሉ ያሉ ማዕድናት ጥናትና ልየታ አቅምን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
ባለፋት ዓመታት በተሠራ የጥናትና ልየታ ሥራ በክልሉ ከ45 በላይ ማዕድናት የተገኙ መሆኑም ተገልጿል።
የሥነ-ምድር ካርታን በተመለከተም ክልሉ 181 ሺህ 190 ኪ/ሜ ስኩዌር ስፋት ያለው ቢሆንም የተጠናው 39 ሺህ ኪ/ሜ ስኩዌር ያህል ብቻ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።
አሁን የተጀመረው ጥናት ሲጠናቀቅ ከ5 ሺህ ኪ/ሜ ስኩዌር በላይ በማጥናት የክልሉን የሥነ-ምድር ካርታ ጥናት ሽፋን ወደ 25 በመቶ ያሳድገዋል ተብሏል።
በክልሉ ለማዕድን ልማት በተሰጠው ትኩረት ከጥናትና ልየታ ጎን ለጎን ግራናይት፣ ጂፕሰም፣ ሲሚንቶ፣ የድንጋይ ከሰልና ሌሎች ማዕድናት የማልማት ሥራ የተጀመረ መሆኑ ተነግሯል።
በየገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የግብር ቢሮ ሃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፥ መንግሥት በጀመረው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ ማዕድን ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፤ በማዕድን ጥናት ዘርፍ ዩኒቨርሲቲዎች እያሳዩት ያለውን ትጋት አድንቀዋል።
የማዕድን ልየታ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ያለውን ተጠቃሚነት ለማስፋት በጥናትና ምርምር መጀመር ለሌሎች ተቋማትም ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ጅምር እንደሆነም ተናግረዋል።
በደሳለኝ ቢራራ