አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ህትመት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ፡፡
ደንበኞቹን የህትመት ጥያቄአቸውን በቴሌብር ሱፐርአፕ በኦንላይን በማከናወን እና ክፍያ በመፈጸም÷ በአዲስ አበባ በሚገኙ 63 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት መታወቂያቸውን መረከብ እንደሚችሉ ተቋሙ አስታውቋል፡፡
በቴሌብር ሱፐርአፕ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ የካርድ ህትመት መተግበሪያ ወይም በድረ ገጽ https://teleprint.fayda.et/ በመግባት÷ የፋይዳ ተለዋጭ ቁጥር (FAN) በማስገባት፣ በአጭር ጽሑፍ የሚላከውን የማረጋገጫ መለያ ኮድ በማስገባት፣ የአገልግሎት ፍጥነት፣ ካርድ የመረከቢያ ቀን እና ቦታ እንደፍላጎታቸው መምረጥ ይችላሉ ተብሏል፡፡
የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተም ደንበኞች በተለያየ የህትመት ማድረሻ ፍጥነት አማራጮች÷ መደበኛ በ7 የሥራ ቀናት (345 ብር)፣ለፕሪሚየም በ2 የስራ ቀናት (600 ብር) እና ለኤክስፕረስ አስቸኳይ (800 ብር) በቀላሉ በቴሌብር ክፍያ በመፈጸም አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡