የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By Feven Bishaw

November 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጸጥታና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ጄነራል አበበ ገረሱ÷ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የነበረው የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የጸጥታ አካላት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው÷በተለይም በሽብር ቡድኑ ሸኔ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡

ይህን ተከትሎም በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ቡድኑ አባላት እጃቸውን ለመንግስት እየሰጡ ነው ያሉት ጄነራሉ÷ ሌሎች አባላትም የቀረበውን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚሰራው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥና የዜጎች ደህንነት ለማረጋገጥ የህብረተሰቡ ጥቆማና ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የጅምላ አፈሳ እየተፈጸመ ነው በሚል የሚሰራጩ መረጃዎችም መሰረተ ቢስ መሆናቸውን ምክትል ሃላፊ ገልፀዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የሚስተዋሉ ግጭቶችን በሰላም ውይይት ለመፍታት አሁንም ቁርጠኛ መሆኑን ምክትል ሃላፊው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ሕዝብ ሰላምን አጥብቆ እንደሚፈልግ አጽንኦት የሰጡት ጄነራል አበበ÷ይህንንም ከሰሞኑ በሰላማዊ ሰልፍ ማረጋገጡን አስታውሰዋል፡፡

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት በሚከናወነው ሥራም ማህበረሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ በመላኩ ገድፍ