የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድል እንጠቀማለን – የቻይና ባለሃብቶች

By amele Demisew

November 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በወታደራዊ ልብስ፣ ጫማ፣ ኮፍያ፣ የጥይት መከላከያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራት ከሚፈልጉ የጂሗ ግሩፕ የቻይና ባለሀብቶች ልዑክ ጋር ተወያዩ ።

በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ሰፊ አምራች ኃይል፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ፣ ለስራ ዝግጁ የሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የታክስ እፎይታ፣ ከቀረጥ ነፃ እድሎችና ለኢንቨስትመንት የተመቻቹ የአሰራር ስርዓቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በጥጥ፣ በቆዳና ለብረት ማዕድን አስፈላጊ በሆነ ጥሬ ሃብት የበለፀገች ሀገር መሆኗን ማስረዳታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ገበያ መግቢያ በር መሆኗ፣ የአፍሪካ ነፃ ገበያ ዕድል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰፊ ተደራሽነት፣ የበርካታ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ መኖሪያ መሆኗ ለዘርፉ ምቹ የገበያ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና ብሪክስን ጨምሮ በበርካታ ዘርፈ-ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ነመሆናቸው ልዑኩ በኢንቨስትመንት ቢሠማራ አሠራሮች እንደሚቀሉለት አስረድተዋል፡፡

ጂሗ ግሩፕ ለቻይና መከላከያ 60 በመቶ የወታደራዊ አልባሳት፣ ጫማዎች፣ ኮፍያ፣ የጥይት መከላከያ አቅራቢ መሆኑን የገለጹት የልዑኩ አባላት÷ በኢትዮጵያ ባለው የኢንቨስትመንት እድል እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡