ዓለምአቀፋዊ ዜና

ኢ-ፍትሐዊ አካሄዶችን ለመፍታት ቅንጅት ያስፈልጋል- ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ

By ዮሐንስ ደርበው

November 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም የሚታዩ ኢ-ፍትሐዊ አካሄዶችንና ጦርነቶችን ለመፍታት ሀገራት በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባ የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አሳሰቡ።

ፕሬዚዳንቱ በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ እየተካሄደ በሚገኘው የቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፍ ተቋማትን የማሻሻል ሥራ ትኩረት እደሚያስፈልገው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የዓለማችን ኢኮኖሚ አግላይና ፍትሐዊ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ በተለይም አዳጊ ሀገራትን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ቻይና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥና በተለይም በአዳጊ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚመጣውን ጫና ለማስቀረት በትብብር እንደምትሠራም አረጋግጠዋል።

ዓለም ሰላምን ትሻለች፤ ለዚህም የቡድን 20 ሀገራት ከፀጥታው ምክር ቤት ጎን ሊቆሙ ይገባል ብለዋል፡፡

በዩክሬን ቀውስና በጋዛ ጦርነት ለዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍን ማድረስ ትኩረት እንደሚፈልግ አንስተው÷ የሁለት ሀገር ፖሊሲን በመተግበር ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ይገባል ነው ያሉት።

በአፈወርቅ እያዩ