አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ በትብብር እየሰሩ እንደሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ፡፡
ሚኒስትር ዴዔታው ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምሥራቅ አፍሪካ ፣ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ምክትል ረዳት ሚኒስትር ቪሰንት ዲ ስፔራ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ በፀጥታ እና ደኀንነት ዙሪያ ስትራቴጂክ ትብብር ያላቸው መሆኑን ገልፀው÷የሀገራቱ ግንኙነት በኢኮኖሚው ዘርፍም ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ያደረገችው ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ የፈጠረ በመሆኑ የአሜሪካ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ሽብርተኝነትን በጋራ በመዋጋት ጠንካራ ትብብር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ያነሱት ሚኒስትር ዴዔታው÷በቀጣይም ትብብሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
በተጨማሪም አምባሳደር ምስጋኑ በሱዳን እና ሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለምክትል ረዳት ሚኒስትሩ ገለጻ አድርገዋል።
ቪሰንት ዲ ስፔራ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሰውበፀጥታ እና ደኀንነት ዙሪያ ያለውን ትብብር የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ቁልፍ ሚና ያላት ሀገር መሆኗን ያነሱት ረዳት ሚኒስትሩ÷በቀጣይ የሁለትዮሽ ግንኙነትቱን በኢኮኖሚ መስክም ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ዙሪያ የአፍሪካ ሕብረት እና የኢጋድ ቅንጅታዊ ሚና ወሳኝ ነው ማለታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡