የሀገር ውስጥ ዜና

ተመድ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ግዳጁን በላቀ ብቃት የሚወጣ መሆኑን ገለጸ

By Mikias Ayele

November 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት ግዳጁን በላቀ ብቃት የሚወጣ ነው ሲሉ በተባበሩት መንግስታት የደቡብ ሱዳን የሰላም ማስከበር ሃይል አዛዥ ሌ/ጄ ምሃን ሰበርማኒያን ገለጹ።

በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል የ18ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ የሜዳልያ ማልበስ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

በፕሮግራሙ የተገኙት የደቡብ ሱዳን የሰላም ማስከበር ሃይል አዛዥ ሌ/ጄ ምሃን ሰበርማኒያን ÷ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቀዳሚ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡

በዘርፉ ከኮሪያ እስከ ደቡብ ሱዳን ባበረከተችው አስተዋፅኦም ለዓለም ሀገራት ምሳሌ መሆኗን ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል ጠንካራና የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ብቃት እየተወጣ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው÷ሠራዊቱ ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ የሚያበረክተው ሁለንተናዊ ድጋፍ ሕዝባዊነቱን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማሃዲ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ሰላም አሰከባሪ ሠራዊት ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ በሰላም  ማስከበር ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በሰላም ማስከበር ብቻ ሳይሆን በመሰረተ ልማትና በዘርፈ ብዙ ድጋፎች ትስስር እንዳላቸው መጥቀሳቸውንም የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡