የሀገር ውስጥ ዜና

ደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምን ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገለጸች

By Mikias Ayele

November 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ  አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢኖንሴባ ሎሲ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን÷ የሁለቱን ሀገራት የቆየና ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ  ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በንግድ፣ ቱሪዝም እና በግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ግንኙነታቸው የበለጠ ለማጠናከር  መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

እየተካሄደ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠረውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች  በተመለከተ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች እድሉን  እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

አምባሳደር ኢኖንሴባ ሎሲ በበኩላቸው÷ በሥራ ዘመናቸው በግብርና፣ ንግድ፣ ቱሪዝም እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ላይ የሁለቱን ሀገራት ሁለገብ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቃል ገብተዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ እያደረገች ያለውን ወሳኝ ሚና አድንቀው÷ በዚህ ረገድ መንግስታቸው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

በውይይታቸው ሀገራቱ በአፍሪካ ህብረት፣ በብሪክስና በተመድ የጋራ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታትና እድሎችን ለመጠቀም ትብብርን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ መምከራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡