የሀገር ውስጥ ዜና

ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በዲጂታል ግብይት በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት ገለፀች

By Feven Bishaw

November 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በዲጂታል ግብይት፣ በባህል ልውውጥና መሰል ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ያላትን ፍላጎት ገልፃለች፡፡

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ጁንግ ጋር የሁለትዮሽ የትብብር ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ሁለቱ ወዳጅ ሀገራት የጠነከረ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው÷ ለኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች የደቡብ ኮሪያ ገበያ ይበልጥ ክፍት እንዲሆንና የሀገሪቱ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንዲሁም የኢትዮጵያን እምቅ አቅም እንዲያስተዋውቁ መልዕክቴን አስተላልፌዋለሁ ሲሉ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል፡፡

አምባሳደር ካንግ በበኩላቸው÷ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር በኢኮኖሚ ትብብር፣ በዲጂታል ግብይት፣ በባህል ልውውጥና መሰል ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎት ገልፀዋል፡፡