የሀገር ውስጥ ዜና

በላይ አርማጭሆ ወረዳ 120 ሜትር ርዝመት ያለው ተንጠልጣይ ድልድይ ተመረቀ

By Melaku Gedif

November 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ 120 ሜትር ርዝመት ያለው ተንጠልጣይ ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።

ድልድዩ ከ22 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

በመሃና ወንዝ ላይ የተሰራው ድልድዩ በግብርና ምርት እምቅ አቅም ያላቸውን ቀበሌዎች ከሌሎች አካባቢዎች ጋር በማስተሳሰር ረገድ ሚናው ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዞኑ በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት በሕብረተሰብ ተሳትፎ 40 ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባቱ የተገለጸ ሲሆን÷ ተንጠልጣይ ድልድዩን ጨምሮ የ3 ድልድዮችን ግንባታ መከናወኑም ተጠቅሷል፡፡

ፕሮጀክቱ በክልሉ መንግስትና ሄልፐስ በተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በ8 ሚሊየን ብር ወጪ መገንባቱን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩ ሌሎች ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለሕብረተሰብ አገልግሎት ክፍት እንዲደረጉም አስተማማኝ ሰላም መፍጠር ወሳኝ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡