አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር (P4G) በ2027 የሚያደርገውን ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ ተመረጠች።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴዔታ ስዩም መኮንን ከዓለምአቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር ዳይሬክተር ሮቢን ማክጉኪን ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይታቸውም የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመመከት በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ ሊያበረክት በሚገባው አስተዋጽኦ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ትብብር በዘርፉ እያደረገ ላለው ተሳትፎም አቶ ስዩም አመስግነዋል።
በፈረንጆቹ 2027 የሚካሄደውን የትብብሩን ጉባዔ እንድታስተናግድ መመረጧም ኢትዮጵያ በዘላቂ የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲጎለብት እየተወጣች ላለው ጉልህ ሚና ዕውቅና የሰጠ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የ አየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎችን ለመቋቋምና ዘላቂ የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ለመገንባት ለሚደረግ ዓለም አቀፍ ጥረት የበኩሏን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ልማት ትብብር በፈረንጆቹ 2017 የተመሰረተ ሲሆን÷ የዴንማርክ፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሜክሲኮ እና ቬትናም መንግሥታት የተመሰረተ አጋርነት ነው።