አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የማህጸን በር ካንሰር በኢትዮጵያ በገዳይነቱ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ያለውን ደረጃ ይይዛል ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
ሚኒስትሯ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር በቱሉ ዲምቱ ቁጥር አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ተገኝተው ሀገር አቀፍ የክትባት ዘመቻውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት÷ በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ ከ8 ሺህ በላይ ሴቶች ለማህጸን በር ካንሰር ተጋላጭ ናቸው።
በመሆኑም በ5 ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በበሽታው ህይወታቸው እንደሚያልፍ ጠቅሰው፤ የማህጸን በር ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ ሁለተኛው ገዳይ የካንሰር በሽታ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሀገር በክትባት መከላከል የሚቻሉ በሽታዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራበት እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት ለሆኑ ሴት ልጆች ከዛሬ ጀምሮ እስከ ህዳር 13/2017 ዓ.ም እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ወላጆች፣ የትምህርት ማህበረሰብ፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ የጎሳ መሪዎች፣ መገናኛ ብዙሃን እና አጋር አካላት ልጆችን ማስከተብ ላይ የግንዛቤ መፍጠር ስራዎች ላይ እንዲሰሩ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።
በዘህ ዘመቻ በሀገርአቀፍ ደረጃ ከ7 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ለሆኑ ሴቶች በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች እየተሰጠ ይገኛል።
በመሳፍንት እያዩ