አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ዘመናዊ እና ወጪ ቆጣቢ የትራንስፖርት ሥርዓትን እውን ለማድረግ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በክልሉ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ትራንስፖርትን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከስዊፍት ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ አቶ ኦርዲን በድሪ እንደገለፁት÷ ከተማዋን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በተለይ በክልሉ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትራንስፖርትን ማሳለጥ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አስገንዝበዋል።
ተሽከርካሪዎቹ ወጪ ቆጣቢ መሆናቸው ማህበረሰቡ ከትራንስፖርት አቅርቦት ጋር በተያያዘ እያቀረበው የሚገኘውን ቅሬታ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።
በሐረር ከተማ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ከተማውን የማይመጥን መሆኑን በማመላከት ወጪ ቆጣቢ እና ለአየር ንብረቱ ተስማሚ እና ምቹ የሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አገልግሎት ለማስጀመር እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የትራንስፖርት ሥርዓቱ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ የሚያጎለብት መሆኑን ጠቁመዋል።
የስዊፍት ቴክኖሎጂ ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ አሸብር በበኩላቸው÷ ቴክኖሎጂው ከተማዋን ለማዘመን እና የሥራ ዕድልን ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይ ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ሀገር ለማስቀረት የሚረዳ መሆኑንጠቁመው÷ ድርጅቱ በክልሉ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ለማድረግ የሚያስችሉ ጣቢያዎችን ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል።
በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ግለሰቦች በ8 ዓመት የሚከፈል የብድር አቅርቦት እንደሚመቻች መጥቀሳቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡