የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በጤናው ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

By amele Demisew

November 18, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን በጤናው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከፓኪስታን የብሔራዊ ጤና አገልግሎት፣ ደንብ እና ቅንጅት ሚኒስትር እና የጠቅላይ ሚኒስትር የጤና ዘርፍ አስተባባሪ ማሊክ ሙክታር አህመድ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በዓለም አቀፍ የጤና ደህንነት፣ በተቋማት ትስስር፣ በተላላፊ እና ወረርሽኝ በሽታዎች መከላከል እና የጋራ ምርምሮች፣ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በፓኪስታን የሕክምና እና ተዛማጅ የጤና ሙያ ትምህርት እድሎችን ማግኘት በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ÷የኢትዮጵያ መንግስት በተለይም ስለ ተላላፊ በሽታዎች፣ ስለ ጤና እና አካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ በመፍጠር የህብረተሰቡን ጤና፣የእናቶችን እና የህፃናትን ሞት በመቀነስና መሰል ጉዳዮች ላይ ያለውን ቁርጠኝነት አብራርተዋል።

የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ አስፈላጊ መሆኑን ማንሳታቸውን በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል ፡፡

ማሊክ ሙክታር አህመድ ባራት (ዶ/ር ) በበኩላቸው ÷በምርምርና ልማት ዘርፍ ትብብር ለመጀመር፣ በጤና ዘርፍ የምርምር ልውውጥ ለማድረግ እና የሕክምና እና ተዛማጅ የጤና ሙያ ትምህርት ለማቅረብ ከኢትዮጵያ ጋር እንሰራለን ብለዋል፡፡