Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ባይደን በሩሲያ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ፈቃድ ሲሰጡ እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጥም – ቭላድሚር ፑቲን

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን ከአሜሪካ የተሰጣትን ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ሩሲያን ለመምታት እንድትጠቀምበት ፍቃድ ሰጥተዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ የሰጡት የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ ተገቢ ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቀዋል።

የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ፤ ፕሬዚዳንት ፑቲን ከወራት በፊት የውጭ ሃይሎች ለዩክሬን ያቀረቧቸው የረዥም ርቀት ሚሳኤሎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ ሊሰጡ እንደሚችሉ እምነታቸውን ገልጸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ኒውዮርክ ታይምስ በስም ያልጠቀሳቸውን የአሜሪካ ባለስልጣንን ምንጭ አድርጎ በሰራው ዘገባ፤ ፕሬዚዳንት ባይደን ዩክሬን በሚሳኤሎቹ የሩሲያን ግዛት እንድትመታ ፈቃድ መስጠታቸውን የሚገልጽ መረጃ መውጣቱን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ፑቲን በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠታቸውን ገልጸዋል።

ለዩክሬን ፈቃድ መስጠት ብቻ ሳይሆን ጥቃቱን ለመፈጸም የውጭ ሃይሎች ድጋፍ ካልታከለበት በስተቀር ዩክሬን በሩሲያ ላይ ጥቃት መሰንዘር እንደማትችል ተናግረዋል።

ቃል አቀባይዋ ፕሬዚዳንቱ ሰጡት ባሉት ምላሽ፥ ትልቁ ጥያቄ ዩክሬን በተሰጣት መሳሪያዎች ሩሲያን እንድትመታ መፈቃዱ ሳይሆን የኔቶ ሀገራት በዚህ ጦርነት ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፉ ወይም እንዳይሳተፉ መወሰን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፑቲን አክለውም ውሳኔው ከተሰጠ ሞስኮ ተገቢ ምላሿን ትሰጣለች ሲሉም ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version