Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሀገራዊ ምክክር ባለቤት ማን ነው?

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 9፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቡድኖች፣ በመንግስት እና በፖለቲካ ሀይሎች መካከል ለተፈጠሩ የሀሳብ ልዩነቶች በውይይት መፍትሔን ለማበጀት የሚከናወን ሂደት ነው፡፡

ሂደቱ በሀሳብ መሪዎች፣ በፖለቲካ ከዋኞች እንዲሁም በሌሎች ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባትን ለማስፈን ያስችላል ተብሎ ይታመናል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ሂደትን የሚያስተባብር እና ሂደቱን በበላይነት የሚመራ ገለልተኛ አካል መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የሂደቱ ባለቤት ማን ነው የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ አስፈላጊ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተቋቋመበት አዋጅ መግቢያ ላይ ሀገራዊ ምክክሮች ተቀባይነት እና ተዓማኒነት ያላቸው እንዲሆኑ ከሚያስችሏቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ምክክሮቹን የሚያመቻቸውና የሚመራው አካል ብቃት እና ገለልተኝነት ነው፡፡

በኢትዮጵያ የሚከናወነውን የምክክር ሂደት ነፃ እና ገለልተኛ በሆነ አካል መምራቱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እና ለዚህም መንግስት ተነሳሽነቱን በመውሰድ ከሕዝብ በሚሰበሰብ ሙዓለ-ንዋይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አቋቁሟል፡፡

ይህም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መንግስት፣ የፖለቲካ እና የሀሳብ መሪዎች እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ሊገለፁ የሚችሉ የማሕበረሰብ መሪዎች የጉዳዩ ባለቤት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ አሳታፊነትን እና አካታችነትን ግንባር ቀደም መርሆዎቹ በማድረግ የተለያዩ ተሳታፊዎችን በውክልና በማሳተፍ ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህ አንፃር ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን ከየሕብረተሰብ ክፍሉ ሲያስመርጥ እና አጀንዳን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሲያሰባስብ የብዙ አካላትን ተሳትፎ እና ውክልና በማረጋገጥ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ሂደቱ ሕዝብ ከሚገኝበት የመጀመሪያው ወይም ቀዳሚ አሃድ የሕብረተሰብ ክፍሎችን፤ በክልል ደረጃ የተዋቀሩ ማህበራትን፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የሲቪክ ማህበራትን ያሳተፈ እንዲሆን ተቀርጿል።

ያንን ተከትሎ የሂደቱ ባለቤት ሕዝብ፣ የተለያዩ ማሕበራት እና ተቋማት እንዲሆኑ ሂደቱ ጠንካራ መሰረት ጥሏል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ሂደት ሊያሳካው የቆመለት ዓላማ አለው፡፡ የምክክር ሂደቱ የተለያዩ ውጤቶችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሊያስገኝ እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም ጥቅል ዓላማው ሀገራዊ መግባባትን ማስፈን ነው፡፡

በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ውጤቶች ለሀገራችን ችግሮች ዘላቂ የመፍትሔ ሀሳቦችን በማመንጨት ረገድ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል፡፡

የዚህ ዋነኛ ተጠቃሚም የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ይህም ሕዝቡን የሀገራዊ ምክክሩ ግንባር ቀደም ባለቤት እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

በርካታ ባለድርሻ አካላት በሂደቱ እየተሳተፉ ባለቤትነታቸውን ሲያዳብሩ ሂደቱም ምሉዕ እየሆነ የተለያዩ ፈተናዎችን መቋቋም ይችላል፡፡

በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ በሀገር ጉዳይ ይመለከተኛል የሚልን ማንኛውም ግለሰብ፣ ቡድን፣ ማህበር ወይም ተቋም ድምፅ (ሀሳብ) ለመስማት ብሎም ለማካተት ይሰራል፡፡

ስለሆነም ሁሉም አካል በባለቤትነት መንፈስ በመነሳሳት ለሀገራዊ መግባባት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ኮሚሽኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

Exit mobile version