የሀገር ውስጥ ዜና

በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ትልማችን ማሳኪያ አንዱ መንገዳችን የስንዴ ልማት ነው -ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

By amele Demisew

November 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ትልማችን ማሳኪያ አንዱ መንገዳችን የስንዴ ልማት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሞረት እና ጅሩ ወረዳ በክላስተር የለማ የስንዴ ማሳን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም በ1ሺህ 465 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የስንዴ ሰብል መመልከታቸውንና ይህም በሶስት ቀበሌዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችን በክላስተር ያስተሳሰር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በክላስተር የለማው ስንዴ በትብብር መስራት አዋጭ መሆኑን ያሳየ ድንቅ ክዋኔ ነው ሲሉም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመላከቱት፡፡

በክልሉ በዘንድሮ ዓመት ከምንጊዜውም በላይ ማዳበሪያን ጨምሮ ከፍተኛ የግብርና ግብዓቶች መሰራጨታቸውን አንስተዋል፡፡

ይህም ለአርሶ አደሮች ምርታማነት ትልቅ ሚና እንዳለው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ሀገር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ አቅማችንን ለማሳደግ ከፍተኛ የምርት ዕድገት ማስመዝገብ ችለናል ነው ያሉት፡፡

በስንዴ ራስን ለመቻል የተቀመጠውን ሀገራዊ ግብ ማሳካታችን የበለጠ አበረታች በመሆኑ ዘንድሮም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጠናከረ ድጋፍ እና ክትትል አድርገናል ብለዋል፡፡