Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሩሲያ የዩክሬን የሀይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ደበደበች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት በይፋ ከተጀመረ ወዲህ ሩሲያ ከፍተኛ የተባለውን የአየር ድብደባ የዩክሬን የሀይል ማመንጫዎችን ኢላማ በማድርግ ጥቃት መፈጸሟ ተነገረ፡፡

በዚህም ሩሲያ 120 ሚሳኤሎችን እንዲሁም 90 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በሁሉም የዩክሬን ግዛቶች ጥቃት መፈጸሟን የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ አስታውቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ሞስኮ የሀገሪቱን የሀይል ማመንጫ መሰረተ ልማቶችን ኢላማ በማድርግ ጥቃቱን መፈጸሟን ነው የገለፁት፡፡

በዚህም ጥቂት በማይባሉ የዩክሬን አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ሀይል መቋረጡን ይፋ አድርገዋል፡፡

በሌላ በኩል ዘሌንስኪ የሀገራቸው አየር መከላከያ 140 የሚጠጉ ኢላማዎችን ማምከኑንም ተናግረዋል፡፡

ሩሲያ በሁሉም የዩክሬን ግዛቶች በሰነዘረችው በዚህ ጥቃት በማይኮላይቭ ግዛት ሁለት ሴቶች የተገደሉ ሲሆን÷ በመካከለኛው ዩክሬን ደግሞ ሁለት የባቡር መንገድ ሰራተኞች መገደላቸውን ሀገሪቱ አስታውቃለች፡፡

በዩክሬን የሚገኝ አንድ ከፍተኛ የሀይል ዘርፍ ኩባንያ የሩሲያ ጥቃት ከፍተኛ ውድመት ማስከተሉን ጠቁሟል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

 

Exit mobile version