የሀገር ውስጥ ዜና

የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ የስበት ማዕከል መሆን በጀመረችበት ወቅት የተካሄደ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Feven Bishaw

November 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል መሆን በጀመረችበት ወቅት የተካሄደ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የከተማችን አንዱ ድምቀት የሆነው 24ኛውን የታላቁ ሩጫ የጎዳና ውድድር ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ ብርቅዬ አትሌቶቻችን እንዲሁም የከተማችን ነዋሪዎች በተገኙበት ዛሬ ማለዳ አስጀምረናል ብለዋል።

ታላቁ ሩጫ ላለፉት 24 ዓመታት ኢትዮጵያን ለዓለም እያስተዋወቀ የቆየ መሆኑን አስታውሰዋል።

የዘንድሮውን ውድድር ለየት የሚያደርገው አዲስ አበባ ተዉባ፣ መንገዶቿ ሰፍተዉ፣ አምረዉና ደምቀዉ ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል መሆን በጀመረችበት ወቅት የተካሄደ መሆኑ ነው ሲሉም ገልጸዋል።