አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ቻይና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(ኮፕ 29) በአዘርባጃን ባኩ መካሄድ ከጀመረ ዛሬ ሰባተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ (Belt and Road Intiative) የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና ተፅዕኖ መቋቋም አላማው ያደረገ ውይይት ተካሂዷል።
በኢትዮጵያና ቻይና የጋራ መድረክ ሁለቱ አገራት ያላቸውን የቆየ ወዳጅነት በአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ላይም በሰፊው በጋራ ለመስራት የሚያግዝ እንደሆነ ተገልጿል።
በጉባኤው ላይ እየተሳተፋ የሚገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የተሻለች ሀገርና ዓለምን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የኢትዮጵያን ልምድና ውጤቶች አቅርበዋል።
ሚኒስትሯ በተለይም ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 40 ቢሊየን ችግኞች እንዲተከሉ ማድረጉን አንስተዋል።
በዚህም መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ሀገራዊ የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደግ መቻሉንና ለበርካታ ዜጎችም አማራጭ የስራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልን እንደ ኬንያ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ ላሉ ጎረቤት ሀገራት በማዳረስም ቀጣናዊ የአረንጓዴ ልማት ትብብር ለማጎልበት ጉልህ አበርክቶ እየተወጣች ነው ብለዋል።
በአዘርባጃኑ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የቻይናን ልዩ ልዑክ የመሩት ሊዩ ዠንሚን ቤጂንግ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በኩል ለአረንጓዴና ለአነስተኛ የበካይ ጋዝ ልማት የምታደርገውን ድጋፍ እንደምታጠናክር አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ሀገራት ከአየር ንብረት ጋር ለተስማሙ የልማት ግቦቻቸው ስኬት ከቀረጿቸው ፕሮጀክቶች ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
ኢትዮጵያና ቻይና በፓሪሱ የአየር ብክለት መጠን ቅናሽ ስምምነት መሰረት ምሳሌ የሚሆን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ትብብር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።