የሀገር ውስጥ ዜና

ኤ.ኤም ሞተርስ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ያመረታቸው ተሽከርካሪዎች ተመረቁ

By Mikias Ayele

November 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በግማሽ ቢሊዮን ብር ወጪ በተገነባው የኤ.ኤም ሞተርስ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በድሬዳዋ ከተማ ያመረታቸው ተሸከርካሪዎች ተመረቁ፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር÷ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በድሬዳዋ በልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት መስክ የሚሰማሩ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል ብለዋል።

ባለሃብቶቹ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት የከተማዋን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች ከማሳደግ ባሻገር ለነዋሪዎች የስራ ዕድል እየፈጠሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተኪ ምርቶችን በማምረት እና ወደ ውጭ ምርቶችን በመላክ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ የሚያስችል ተግባር እየፈጸሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ባለሃብቶች የጀመሯቸው ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ አስተዳደሩ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚያጠናክር የገለፁት ከንቲባው÷ አስተዳደሩ ፈጣን አገልግሎት በመስጠትና የመሬት አቅርቦት በማመቻቸት ድጋፍ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

የኤ.ኤም ሞተርስ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ኦብሳ አህመድ በበኩላቸው÷ ባለፈው ዓመት ወደ ስራ የገባው ፋብሪካቸው 150 ቋሚ እንዲሁም 100 ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡