Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ማዕከሉ ሰላምና ፍትህ ለማስፈን ተጨማሪ አቅም የሚሆን ነው – ኮ/ጄ ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና ምርምር ልህቀት ማዕከል አስተማማኝ ሰላምና ፍትህ ለማስፈን ለሚከናወኑ ስራዎች ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና ምርምር ልህቀት ማዕከልን መርቀው ከፍተዋል፡፡

ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በምረቃው ወቅት፤ ማዕከሉ ከአፍሪካ ትልቁ የፖሊስ ፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል ነው ብለዋል፡፡

የማዕከሉ መገንባት ቀደም ሲል ተበታትነው ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን ወደ አንድ ማምጣቱን ገልጸው፤ በዋናነት የሰነድ፣ የጦር መሳሪያ፣ የቃጠሎ አደጋ፣ የፍንዳታ፣ የዘረመል ወይም ዲኤንኤ፣ የዲጂታል ፎረንሲክ፣ የኬሚስትሪና የስውር አሻራና መሰል ለወንጀል ምርመራ ስራ አስፈላጊ የሆኑ የምርመራ ላብራቶሪዎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡

ማዕከሉ የምርመራ ስራ ብቻ ሳይሆን በፎረንሲክ ምርምር ብቁ የሆነ የሰው ሃይል የማፍራት ኃላፊነት እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

የክልል የፖሊስ አቅምን ለመገንባት ለሙያው ብቁ የሆኑ ወጣቶችን በመመልመል ቁጥራቸው ከፍ ያሉ ሰልጣኞችን ተቀብሎ ለማሰልጠን የሚችል ደረጃውን የጠበቀ ስፍራ መዘጋጀቱንም መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያን ድጋፍና ዕገዛ ለሚፈልጉ የአፍሪካ ሀገራትና በፎረንሲክ ሙያ የበቁ ዓለም ላይ ያሉ ምሁራን ስልጠናና ምርምር የሚያደርጉበት ሆኖ መመቻቸቱንም ጠቁመዋል፡፡

Exit mobile version