የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ተካሄደ የሚባለው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሳተፉበት ነው – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

By ዮሐንስ ደርበው

November 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ተካሄደ የሚባለው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሳተፉበት መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡

ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም መቀሌ፣ አክሱም፣ አዲግራት እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ75 በላይ የሚሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰብ አባላት ጋር በአዲስ አበባ ተወያይቷል፡፡

በመድረኩ መስፍን አርአያ (ፕ/ር)፥ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ተካሄደ የሚባለው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሲሳተፉበት ነው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ምክክር የትግራይ ክልልን የሚያካትት በመሆኑ ክልሉ የሚሳተፍበትን ሁኔታ ለመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ትግራይ ክልልን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ አሳታፊና አካታች ምክክር ለማካሄድ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የክልሉ ህዝብ ሃሳቦች ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ያነሱ ሲሆን፥ ኮሚሽኑ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እንደ ድልድይ ሆኖ በማገልገል ሚናውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

መንግስት የትግራይ ክልል ህዝብ ችግሮችን ትኩረት ሰጥቶ እንዲፈታ ኮሚሽኑ ጫና ማድረግ እንደሚኖርበትም አክለዋል፡፡

በትግራይ ክልል ምክክር ለማድረግ በመጀመሪያ መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ተሳታፊዎቹ ፥ ለዚህም ህዝቡ የሚሰማውን ግልፅ አድርጎ የሚናገርበት መድረክ ሊመቻችለት ይገባል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ እንደ ገለልተኛ ተቋም ህዝቡ ጋር ወርዶ በማወያየት ያጋጠሙ ችግሮች እንዲፈቱ የሚያስችል ከሆነ በትግራይ ክልል የምክክሩን ሂደቶች ለማካሄድ መንገድ እንደሚከፍትለትም ነው ተሳታፊዎቹ የጠቆሙት፡፡