አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 19ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ከኮርፖሬት ያነጋገራቸው የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የዘንድሮው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ ይከበራል።
ክልሉ በአዲስ መልክ በተደራጀ ማግስት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከበር በዓል በመሆኑ በልዩነት እንደሚጠቀስ አስተያየት የሰጡ የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
በዚህም በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በከተማዋ ከሚገኙ ቀበሌዎች የተወጣጣ አስተባባሪ ኮሚቴ ተዋቅሮ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
በተለያዩ ሁነቶች በዓሉን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም አስታውቀዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን እና ወንድሙ አዱኛ