የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ሀገራዊ ሪፖርት መሰረት አድርጎ በትሮይካ የሦስትዮሽ ቡድን የተዘጋጀው ሪፖርት ጸደቀ

By ዮሐንስ ደርበው

November 16, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በ4ኛው ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግምገማ መድረክ ላይ ያቀረበችውን ሀገራዊ ሪፖርት መሰረት አድርጎ በትሮይካ የሦስትዮሽን የተዘጋጀው የተጠናቀረ ሪፖርት ጸድቋል፡፡

ኢትዮጵያ በ4ኛው ዙር የተባበሩት መንግስታት ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግምገማ 47ኛው መደበኛ ስብሰባ ላይ በ3ኛው ዙር የግምገማ መድረክ የተሰጧትን ምክረ ሀሳቦች ከመተግበር አንጻር ያከናወነቻቸውን ተግባራት አስመልክቶ ሕዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም ሪፖርት ማቅረቧ ይታወሳል።

በስዊዘርላንድ ጄኒቫ እየተካሄደ በሚገኘው ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግምገማ መድረክ በፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ የተመራ ልዑክ እየተሳተፈ ነው፡፡

በመድረኩ ላይም ላለፉት 5 ዓመታት የሰብዓዊ መብት አጠባበቅን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያከናወነቻቸውን ተግባራት አስመልክቶ ሀገራዊ ሪፖርት ማቅረብ ጀምሯል፡፡

በዚህም የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮጵያን ሪፖርት መሰረት አድርጎ የተደረገውን አካታች ውይይት ለማጠናቀር የተሰየመው የትሮይካ የሦስትዮሽ ቡድን ያጠናቀረው ሪፖርት ልዑካን ቡድኑ ተመልክቶ አስተያየት እንዲሰጥበት ከተደረገ በኋላ ትናንት ጸድቋል፡፡

በመድረኩ ከ115 በላይ ሀገራት ለኢትዮጵያ 316 ምክረ ሀሳቦችኝ ያቀረቡ ሲሆን ፥ ሀገሪቱ ከታህሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በፊት የተቀበለቻቸውን ምክረ ሀሳቦች ለይታ ታሳውቃለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡