Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔን ለማስተናገድ የሚደረገው የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተገመገመ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እና የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዝግጅት አስተባባሪ ብሔራዊ ኮሚቴ ሁለተኛ ዙር የዝግጅት ሥራ አፈጻጸም ግመገማ አድርጓል፡፡

በመድረኩ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ዋና መስሪያ ቤት መገኛ እና አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ዘንድሮ የሚካሄደውን የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጀት ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶች መደረጋቸው ተገምግሟል።

በተጨማሪም ተቋማት በብሔራዊ ዝግጅት ኮሚቴው አማካኝነት የተሰጡ እቅዶች አፈፃፀማቸው፤ ከተቋማቸው ባህሪ አንፃር መነሻ እና ዝርዝር እቅዶች ቀርበው ውይይት ተካሄዶባቸዋል።

ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ስለሚያስችል የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና እንዲሁም ደኀንነቱ የተጠበቀ የላቀ አገልግሎት ለመስጠት የተሟላ ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

ጉባዔውን ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ለማድረግ የወጡ እቅዶች በአፈፃፀም እና በትግበራ ምዕራፍ የተዋጣለት እንዲሆን መስራት እንደሚገባ ተመላክቷል።

38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም እንዲሁም 46ኛው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ደግሞ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

Exit mobile version