Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአክስቱን ልጅ በሸኔ ታግቷል በማለት ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገና ከወላጆቹ ገንዘብ የተቀበለው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)የአክስቱን ልጅ በሸኔ ታግቷል በማለት ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገና ከወላጆቹ ገንዘብ የተቀበለው ግለሰብ በ21 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ወንጀል ችሎት ወሰነ።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ ዐቃቤ ሕግ ያዕቆብ አሸናፊ በተባለ ግለሰብ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 539 (1) (ሀ) ላይ የተደነገገውን እና የወንጀል ህግ አንቀጽ 692 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተደነገገውን ተላልፏል በማለት ክስ አቅርቦበት ነበር።

በቀረበው የክስ ዝርዝር ላይ ዐቃቤ ሕግ እንዳመላከተው፤ ተከሳሽ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ቦኖ አይገዶ ቀበሌ ልዩ ቦታው መድሐኒአለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ወደ ሚገኘው ጫካ የአክስቱን ልጅ የሆነውንና ዕድሜው 14 ዓመት የሆነውን ሟች ሕጻን ሀብታሙ ተሾመን ከዚያ ቀደም መቶኛል በሚል ቂም በመነሳሳት ስልክ በመደወልና የስልክ ሚሞሪ እሰጥሀለው ብሎ በማባበል ወደ ጫካው እንዲመጣ በመጥራትና በመጠበቅ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ህይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል።

ከዚህም በኋላ የሟቹን አስከሬን ጫካ ውስጥ ደብቆ ከሟች ቤተሰቦች ጋር ሟች በሸኔ ታግቷል በማለት አፋላጊ መስሎ አብሮ ሲያፈላልግ ከቆየ በኋላ ከአካባቢው የተሰወረ ሲሆን÷ የሟች ቤተሰቦች ሟችን ለማግኘት ባደረጉት ብርቱ ፍለጋ ከ10 ቀናት በኋላ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም አስክሬኑ በአውሬ ተበልቶ ለብሶት የነበረው ልብስ እና የጭንቅላቱ ቅሪት ጫካው ውስጥ ሊገኝ መቻሉ ተጠቅሶ ተከሳሽ ሆነ ብሎና አስቦ በፈጸመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ተከሷል፡፡

በሁለተኛ ክስ ደግሞ ተከሳሹ የተጠቀሰውን የግድያ ወንጀል ድርጊት ከፈጸመ በኋላ ከሟች ቤተሰቦች ጋር አብሮ የሚያፈላልግ በመምሰል አብሯቸው እየዞረ የሟችን ስልክ በመጠቀም ሟችን በሸኔ ታግቷል ልጃችሁን ከፈለጋችሁ 25 ሺህ ብር አምጡ ብሎ በመጠየቅና “ጅቱ ድሪባ የሸኔ ኃላፊያቸው ናት በማለት እና በባለቤቱ በስሟ በተከፈተ የኦሮሚያ ባንክ ሂሳብ ውስጥ አስገቡ” በማለት ወደ ወላጅ አባቱ እና ወንድሙ ጋር በኦሮሚኛ ቋንቋ መልእክት ጽፎ የላከ መሆኑ በክሱ ተገልጿል።

በዚህ መልኩ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰዓት የሟች ወንድም በተጠቀሰው ሂሳብ ቁጥር 25 ሺህ ብር ቢያስገባም እንደገና “ብሩ አይበቃም አለቃችንን አስቀይማችኋል” በማለት ተጨማሪ ብር ጠይቆ ለሟች ወላጅ አባት “ጥር 28 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ በግምት 4፡00 ሰዓት በምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ቦኖ አይገዶ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ልዩ ቦታው መድሐኒዓለም ቤተ-ክርስቲያን የታቦት ማደሪያው ጋር ካለው ቄሶች ከሚቀመጡበት ባዶ ቤት አስቀምጥ “በማለት ስልክ ደውሎ ያዘዘና ተጨማሪውን ማለትም 10 ሺህ ያስቀመጠለት እራሱ የወሰደው ሲሆን በድምሩ 35 ሺህ ብር ከሟች ቤተሰቦች በማታለል የወሰደ መሆኑ ተጠቅሶ የማታለል ወንጀል ተከሷል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ከክስ ዝርዝሩ ጋር ዘጠኝ የሰው ምስክርና አምስት የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ ያቀረበ ሲሆን÷ ተከሳሹ የክስ ዝርዝሩ በችሎት እንዲደርሰው ከተደረገ በኋለ የወንጀል ድርጊቱን አምኖ ቃሉን መስጠቱን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበታል።

ከዚህም ፍርድ ቤቱ በኋላ የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ አስተያየት በመያዝ ተከሳሹን ያርማል ሌላ ሰውንም ያስተምራል በማለት በ21 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version