የሀገር ውስጥ ዜና

ተቋማቱ የሥራ ርክክብ አደረጉ

By amele Demisew

November 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ከተማ መብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን የሥራ ርክክብ ፈጸሙ።

በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የአዳስ አበባ መንገዶች ባለስልጣንና ዋና ዳይሬክተር ሙዲን ረሻድ (ኢ/ር)፤ የመንገድ ዳር መብራቶች ከመንገድ መሰረተ ልማት ጋር ሲተዳደሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ነገር ግን የመንገድ ዳር መብራቶች አስተዳደር አዲስ ለተቋቋመው የአዲስ አበባ ከተማ መብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን መተላለፋቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰብስቤ ሁሴን በበኩላቸው፤ የከተማዋን ገፅታ ይበልጥ ለመቀየርና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ባለስልጣኑ መቋቋሙን አንስተዋል።

በዚህም ባለስልጣኑ የመንገድ ላይ መብራቶችን ይተክላል፣ ያድሳል፣ ስታንዳርዶችን ያዘጋጃል እንዲሁም ያስተዳድራል ብለዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር) ባለፉት ዓመታት የተተከሉ መብራቶች መዲዋን ደህንነቷ የተጠበቀ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህንን ያስቻሉ መሰረተ ልማቶች ሳይጠፉና ሳይቆራረጡ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በባለቤትነት መንፈስ መጠበቅና ማደስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ይህን ለማሳካትና ከተማዋን የውበትና ብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ እንዲቻል በከተማው መንገዶች ባለስልጣን አንድ ክፍል ይመራ የነበረው ዘርፍ እራሱን ችሎ እንዲቋቋም መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በመራኦል ከድር