ስፓርት

ፖል ፖግባ በ2025 ወደ ሜዳ ይመለሳል

By Mikias Ayele

November 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ፈረንሳዊው አማካይ ፖል ፖግባ ከቅጣት መልስ በፈረንጆቹ 2025 ወደ እግር ኳስ ሜዳ እንደሚመለስ ተገለፀ፡፡

የ31 ዓመቱ አማካይ ከማንቼስተር ዩናይትድ ወደ ጁቬንቱስ ካቀና በኋላ የተከለከለ ንጥረ ነገር ተጠቅሞ መገኘቱን ተከትሎ ለአራት አመታት በማንኛውም ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፍ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡

ሆኖም ግን በፈረንጆቹ 2023 የተላለፈበት የአራት ዓመት ቅጣት በዓለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት አማካኝነት ወደ 18 ወራት ዝቅ እንዲል በመደረጉ ወደ ሜዳ ሊመለስ መሆኑ ተነግሯል።

በዚህም ፖግባ በፈረንጆቹ 2025 ወደ እግር ኳስ ይመለሳል የተባለ ሲሆን ከአሊያንዝ ስንብት በኋላ ቀጣይ የሚያርፍበት ክለብ አለመታወቁን ያሁ ስፖርት ዘግቧል፡፡

ፖል ፖግባ በዛሬው እለትም ከጁቬንቱስ ጋር ያለውን የኮንትራት ውል በስምምነት ለማቋረጥ መስማማቱ ተገልጿል፡፡

የኮንትራት ዉሉ የተቋረጠው የጁቬንቱሱ አሰልጣኝ ቲያጎ ሞታ በቅጣት ላይ የሚገኘውን ፈረንሳዊ አማካይ አለመፈለጋቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም ጁቬንቱስ በውድድር ዓመቱ ለፖግባ የሚከፍሉትን 10 ሚሊየን ዩሮ ማስቀረት እንደሚችሉ ነው የተገለፀው፡፡