አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡
በድሬዳዋ ከተማ የኢንዱስትሪ ልምድ ማሰራጫ መድረክ ላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት÷ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ለተጀመረው የብልፅግና ጉዞ ወሳኝ ነው።
የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ምርታማነትና ውጤታማነት ለማሳደግ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ ፈጠራዎችን ወደ ስራ ለማስገባትና የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ አመልክተዋል።
በገጠርም ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የድሬዳዋ ከተማ የኢንዱስትሪ ማዕከልና ለወደብ ቅርብ በመሆኗ በከተማዋ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በዚህ ዓመትም በከተማዋ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማሳደግ 1 ሺህ 200 ካሬ ሜትር ቦታ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
በነስሪ ዩሱፍ