አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጋምቤላ ክልል በተያዘዉ በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ብቻ ከ900 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል፡፡
ክልሉ በሩብ ዓመቱ 325 ኪሎግራም ወርቅ ገቢ ለማድረግ ያቀደ ቢሆንም ከ900 ኪሎግራም በላይ ወርቅ ገቢ በማድረግ ከዕቅዱ በላይ ማሳካት መቻሉ ተመላክቷል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዉን ተከትሎ በኮንትሮባንድ ይወጣ የነበረ ወርቅ ወደ ብሄራዊ ባንክ እንዲገባ እድል በመፈጠሩ ይህ ልዩነት መምጣቱን የክልሉ ማዕድን ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ኤሊያስ ገዳሙ ተናግረዋል።
በሶስት ወር ለብሔራዊ ባንክ የገባዉ የወርቅ መጠን ከአምናዉ ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ844 ኪሎ ግራም ብልጫ ያለዉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረዉ የወርቅ ግብይት ዋጋ ኮንትሮባንድን የሚያበረታታ እንደነበር አስታውሰው፤ በዚህም ለብሔራዊ ባንክ ይገባ የነበረ የወርቅ ምርት ዝቅተኛ እንደነበር አስረድተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ህገ ወጥ ግብይት እንዲዳከምና ምርቱ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል በአራት ወረዳዎች የወርቅ ማዕድን የሚመረት ሲሆን ሌላ ተጨማሪ 5ኛ ወረዳ ወርቅ ወደ ማምረት ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአብዱ ሙሃመድ