አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች የፓኪስታን ባለሃብቶችን ለማስተናገድ ያላትን ዝግጁነት ገለጸች።
በራዋልፒንዲ ንግድ ምክር ቤትና ኢንዱስትሪ የቢዝነስ ፎረም ላይ የተገኙት በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ÷የፓኪስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ዕድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ወደተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ መግባቷን ጠቅሰው፤ ይህም ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።
ንፁህና አረንጓዴ ኃይል እንዲሁም በሰለጠነ የሰው ኃይል ረገድ ለፓኪስታን ኩባንያዎች አንጻራዊ ጠቀሜታ እንደምትሰጥም አስረድተዋል።
በመሆኑም የፓኪስታን ባለሃብቶች በመድሐኒት፣ ህክምና መሣሪያዎች፣ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን ቁፋሮ፣ ቱሪዝም እና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን ጨምሮ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች መሰማራት እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ ባለሃብቶቹን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን በመግለፅ ጥሪ አቅርበዋል።
የራዋልፒንዲ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኡስማን ሻውካት በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በፓኪስታን ባለሃብቶች ተመራጭ መሆኗን ገልጸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማሳደግ ረገድ የንግድ ምክር ቤቱ ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።