የሀገር ውስጥ ዜና

ከኢትዮጵያ ጋር ያለኝን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ እፈልጋለሁ – ብራዚል

By Feven Bishaw

November 15, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና ብራዚልን ዘርፈ-ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠሩ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳሲልቫ አረጋገጡ፡፡

በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳሲልቫ አቅርበዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ከብራዚል ጋር በኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ቱሪዝም እና ግብርና ላይ ያላትን የቆየ ግንኙነት ማጠናከር እና የሁለትዮሽ ግንኙነቷን ወደ ላቀ የስትራቴጂያዊ አጋርነት ማሳደግ እንደምትፈልግ አምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እየተገበረችው ስላለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ተግባራት እና ሌሎች የሪፎርም ሥራዎችን አብራርተዋል፡፡

ሁለቱም ሀገራት የብሪክስ አባል መሆናቸው በንግዱ ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት በይበልጥ ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ተቋማት ማሻሻያ እና የጋራ አጀንዳዎች ላይ በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት መስፋፋት፣ የልማት ፋይናንስ በማሰባሰብ፣ ድህነትንና ረሃብን በማጥፋት እና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ላይ በቅርበት በመሥራት ትብብሯን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በበኩላቸው÷ በቅርቡ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ላደረጉላቸው አቀባበል ምሥጋና አቅርበው የሁለቱን ሀገራት ዘርፈ-ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለይም በኢኮኖሚውና በግብርና ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በትጋት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡