አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2017 ዓ.ም (ኤፍ ቢ ሲ)ፍሬው ሺበሺ በሃያ ሁለት ዓመት እድሜው ባጋጠመው የሞተር ሳይክል አደጋ የአንድ ዐይን ብርሀኑን እንዳጣ ይናገራል።
የዐይን ብርሃኑ እንዲመለስ የተለያዩ ህክምናዎችን ሲያደርግ ቢቆይም መፍትሄ ሳያገኝ አስራ ሁለት ዓመታትን አሳልፏል።
በወቅቱ በአንድ ዐይኑ ብቻ የተለመደ የህይወት እንቅስቃሴውን ለማከናወን ተቸግሮ እንደነበር የሚገልፀው ፍሬው በርካታ ፈታኝ ጊዜያትን እንዳሳለፈ ያስታውሳል።
መፍትሄ አልባ በሆኑ ሙከራዎች ተሰላችቶ ተስፋ በቆረጠበት አንድ ወቅት ታድያ ቤተሰቦቹ ባደረጉበት ግፊት ወደ ዳግማዊ ምኒሊክ አጠቃላይ ሆስፒታል ያመራል።
በዚያም በተደረገለት የዐይን ብሌን ንቅለ ተከላ ዳግም ብርሃን ማግኘት መቻሉን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።
ከረጅም ጊዜ የእይታ ችግር በኋላ ዳግም ማየት የቻለው ፍሬው እንደአዲስ የተፈጠርኩ ያህል ነው የተሰማኝ በማለት ደስታውን ይገልፃል።
ፍሬው ሺበሺ ማንነቱን ሳያውቅ የዐይን ብሌኑን በመለገስ ብርሃኑ እንዲመለስ ላስቻለው በጎ ፈቃደኛ ምስጋናውን ሲያቀርብ የለጋሹ ነፍስ በሰላም እንድታርፍ የዘወትር ጸሎቱ እንደሆነም ይናገራል።
መዳን እየቻሉ በዐይን ችግር የሚሰቃዩ ሰዎችን ብርሀን መመለስ የሚያስችለውን የዐይን ብሌን መቅበር የለብንም የሚለው ፍሬው ሰዎች ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ለመለገስ ቃል በመግባት የሰዎችን ሕይወት መቀየር እንዲችሉ መልዕክቱን አስተላልፏል።
የዐይን ብሌን ለጋሾች ወር እስከ ህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚከበር የገለፀው የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የዐይን ብሌን ለመለገስ ቃል እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል።
በበፀሎት መንገሻ