አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው በተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የመንግስት አፈፃፀም ክፍል ሃላፊ በመሆን የተሾሙት ኤሎን መስክ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የኢራን ልዩ መልዕከተኛ አሚር ሰኢድኢራቫኒ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በግልጽ ባልተነገረ መንገድ የተካሄደው ውይይቱ በቴህራን እና በአሜሪካ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር መካከል መካከል በሚኖረው ግንኙነት ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተነግሯል።
በውይይቱ የተሳተፉ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የአሜሪካ ባለስልጣናት÷ ውይይቱን አዎንታዊ እና የምስራችን ይዞ የሚመጣ ነው ሲሉ ገልፀውታል፡፡
ትራምፕ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው አሜሪካ ከ2015ቱ የኢራን የኑክሌር ስምምነት እንድትወጣ ያደረጉ ሲሆን በኢራን ላይ ጠንካራ ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡
በዛሬው እለት የተደረገው ውይይት ትራምፕ በኢራን ላይ ያላቸውን ፖሊሲ በአዲስ መልኩ እንዲያዩት የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በጉዳዩ ላይ የኢራን ባለስልጣናት የሰጡት አስተያይት የለም መባሉን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
ከኢራን ጋር ንግግር ያደረጉት የኤክስ እና የተስላ ኩባንያ ባለቤቱ የዓለም ቁጥር አንድ ባለሃብት ኤሎን መስክ በፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የመንግስት አፈፃፀም ክፍል ሃላፊ በመሆን እንዲያገለግሉ መሾማቸው ይታወቃል።