አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ቃል የገባችባቸውን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶች በሙሉ ቆጥራ የምታስረክብ ሀገር እንደሆነች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ገለፀ፡፡
ከዱባይ እስከ ባኩ ያለፈውን አንድ አመት ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሰራቻቸውን ስራዎች በተመለከተ በኢትዮጵያ ፓቪሊዮን ከአጋር ድርጅቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ ከፖሊሲ ለውጥ ጀምሮ በአረንጓዴ አሻራ፣ በታዳሽ ሀይል እንዲሁም በምግብ ሰብል እራስን ለመቻል በርካታ ስራዎችን እየሰራች እንደሆነ ገልጸዋል።
ባለፈው የተመድ የአየርንብረት ለውጥ ጉባዔ ኮፕ28 የተገቡ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነቶችንም መፈፀሟን ተናግረዋል ፡፡
የልማት አጋር ድርጅቶቹ በበኩላቸው÷ ዓለም የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን ለመሸፈን የሀይል አማራጮችን ሙሉ በሙሉ በታዳሽ ሀይል ለመተካት የያዘውን እቅድ ኢትዮጵያ ቀድማ ጀምራለች ነው ያሉት፡፡
በተለይም በአረንጓዴ አሻራ እየተሰራ ያለው ስራ ለተቀረው ዓለም ምሳሌ መሆን የሚችል መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ እየሰራችው ላለችው ስራ ድጋፍ እናደርጋለን ማለታቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡