አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያው የሚታይ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበበት መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ ገለጹ፡፡
የባንኩ ገዥ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ 100 ቀናትን የተሻገረው የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በነዚህ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ ጊዜያትም የታዩ መልካም ውጤቶች በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ አዲስ መነቃቃት መፍጠሩን ነው ያነሱት፡፡
በተለይም ከውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ ጋር በተያያዘ እንደ ሀገር በብሔራዊ ባንክ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ ስለማደጉ አረጋግጠዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መተግበር በጀመረበት ዕለት የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር እንደነበር አስታውሰው÷ በአሁኑ ወቅት ክምችቱ 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላርን ተሻግሯል ነው ያሉት፡፡
የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ እንዲያድግ በሪፎርም ትግበራው የተገኘ ድጋፍና ብድር እንዳለ ሆኖ የወርቅ የወጪ ንግድ ማደግ ትልቁን አስተዋጽዖ አበርክቷል ያሉት ገዥው÷ ክምችቱ በይበልጥ እየተሻሻለ እንደሚሄድ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ሌላኛው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ስኬት መገለጫ በአጠቃላይ በባንክ ዘርፉ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት እድገት መሆኑን ጠቁመው÷ በግል ባንኮች ጭምር ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት በ3 ወራት ውስጥ ከፍተኛ እድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት 3 ወራት ውስጥ በባንክ ስርዓት ውስጥ ከኤክስፖርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪን በተመለከተም በአማካይ ባንኮች በየወሩ ወደ 500 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንደነበራቸው አንስተዋል፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት 3 ወራት ባንኮች በአማካይ ወደ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር መግዛታቸውን በመግለጽ÷ ወደ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለሚፈልግ ሰው መሸጥ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
አቶ ማሞ ባንኮች ከዚህ ቀደም የነበረባቸውን የውጭ ምንዛሪ እዳ ሳይቀር መክፈል መቻላቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ባንኮች ኤል ሲ ተከፍቶ ሳይከፍሉት የቆዩት ከ500 ሚሊየን ዶላር በላይ የተከማቸ ዕዳ ሙሉ በሙሉ ከፍለው ከዕዳ ነጻ ሆነዋል ከዚህ በኋላ ለአዲስ ኤል ሲ ክፍያ መክፈል ነው የሚጠበቅባቸው ሲሉም አብራርተዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ እያንዳንዱን የንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ሀብት እና እዳ በየጊዜው እንደሚገመግም አንስተው÷ አሁን ላይ የንግድ ባንኮች ያሉበት ደረጃ የውጭ ምንዛሪ ስርዓቱ እየተረጋጋ እንደሚሄድ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል እንደ አዲስተ የተጀመረው እና ትልቅ ውጤት እንደሚመጣበት ተስፋ የተጣለበት ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የሚበዳደሩበት ስርዓት ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡
የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ያላቸው ባንኮች የውጭ ምንዛሪ እጥረት ላለባቸው ባንኮች መሸጥ የሚችሉ ሲሆን÷ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በባንኮች መካከል 100 ሚሊየን ዶላር ሽያጭ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህን በባንኮች መካከል የሚፈጸም የውጭ ምንዝሪ ሽያጭና ግብይት በቴክኖሎጂ ለማገዝ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
በውጭ ምንዛሪ ላይ እየታየ ያለው ለውጥ ሪፎርሙ በትክክለኛ መንገድ ላይ ስለመሆኑም ያሳያል ነው ያሉት፡፡
በባሃሩ ይድነቃቸው እና በረከት ተካልኝ