የሀገር ውስጥ ዜና

ደን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያለውን ሚና ለማሳደግ ምርምር እየተካሄደ መሆኑ ተጠቆመ

By ዮሐንስ ደርበው

November 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የደን ሃብት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያለውን ሚና ለማሳደግ የሚያስችል ጥናትና ምርምር እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም እንዳሉት፥ የደን ሽፋን መጠንን ለማሳደግ በትኩረትና በትብብር እየተሰራ ነው።

በተለይም ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በዘርፉ አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን ተከትሎም የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ምጣኔ ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን አንስተው፤ በፈረንጆቹ 2030 የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ምጣኔ 30 በመቶ ለማድረስ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

እቅዱን በስኬት ለማጠናቅም በዘርፉ ውጤት የሚያስገኙ ጥናትና ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑን ነው የጠቀሱት።

ምርምሮቹ በኢትዮጵያ ደን ልማት ሒደት የሚስተዋሉ ተግዳሮቾችን በመለየት ዘርፉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያለውን ሚና የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተተከሉ ችግኞች ለውጤት እንዲበቁ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተለይም በተለያዩ አካባቢዎች የተተከሉ ችግኞች በበጋ ወቅት የውሃ እጥረት እንዳይገጥማቸው የሚመለከታቸው አካላት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በታሪኩ ወልደሰንበት