ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ በሩሲያ ድንበር አቅራቢያ አዲስ የሚሳኤል ማዘዣ ጣቢያ ከፈተች

By Mikias Ayele

November 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በሩሲያ ድንበር አቅራቢያ አዲስ የሚሳኤል ይዞታ ማቋቋሟን አስታወቀች፡፡

በሰሜን ምዕራብ ፖላንድ እና በባልቲክ ባህር አጠገብ በምትገኘው ሬዲዚኮ ከተማ የተገነባው አዲሱ የባላስቲክ ሚሳኤል ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ በማዕከላዊ አውሮፓ የመጀመሪያው የአሜሪካ ቋሚ ወታደራዊ ይዞታ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በሰሜን ምዕራብ ፖላንድ የምትገኘው የሬድዚኮ ከተማ ደግሞ ከሩሲያ ካሊንግራድ ግዛት በ160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን ሩሲያ በአካባቢው ጠንካራ ወታደራዊ መሰረቶች አሏት ተብሏል፡፡

የፖላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራዶስላው ሲኮርስኪ÷ የአሜሪካ የባላስቲክ ሚሳኤል ማዘዣ ጣቢያ ግንባታ በአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት በነበሩት ጆርጅ ደብሊዩ ቡሽ፣ ባራክ ኦባማ እና ዶናልድ ትራምፕ ተጀምሮ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ተጠናቋል ብለዋል፡፡

የወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ፕሮጀክቱ የአሜሪካ ጂኦ ስትራቴጂክ ወጥነትን ያሳያል ያሉት ሚኒስቴሩ÷ ይህም የአሜሪካ እና የፖላንድን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በቀድሞ የስልጣን ዘመናቸው ለሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አስፈላጊውን ድጋፍ አለማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የሩሲያን ማጥቃት ይሁንታ የመስጠት ያህል ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡

ከኔቶ አባል ሀገራት ውስጥ አሜሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ስትሆን የድርጅቱ ሌሎች አባል ሀገራት ከነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ለወታደራዊ ሀይል ከሚያወጡት ሁለት በመቶ ድጋፍ በላይ አሜሪካ ከፍተኛውን የወታደራዊ ሀይል ድጋፍ ታደርጋለች፡፡