የሀገር ውስጥ ዜና

ውል ተፈጽሞባቸው ሰው ያልገባባቸው በዕጣ የተላለፉ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች መጨረሻ …

By ዮሐንስ ደርበው

November 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ዓመታት በ20/80፣ 40/60 እና በጨረታ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ተላልፈው ውል ቢፈጸምባቸውም እስከ አሁን ዕድለኞች ያልገቡባቸው በመኖራቸው “ለሕገ-ወጥ ድርጊት” እየዋሉ መሆኑ ይነሳል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት “በዕጣና በጨረታ ተላልፈው ውል የተፈጸመባቸው እና ነዋሪ ያልገባባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጉዳይ ከምን ደረሰ?” ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንን ጠይቋል።

ምንም እንኳን ዕድለኞች በዕጣም ሆነ በጨረታ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ደርሷቸው ውል ቢፈጽሙም÷ በአንዳንድ ሳይቶች በመሠረተ-ልማት አለመሟላት ምክንያት ለመግባት እንደሚቸገሩ ማንሳታቸውን፣ እንደተባለው የመሠረተ-ልማት ችግር ካለ እየተሠጠ ያለ ጊዜያዊ እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲሁም ወደ ቤት መግባት ያልፈለጉ ወገኖች መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል የሚሉ ጥያቄዎችን ለኮርፖሬሽኑ አንስተናል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሽመልስ ታምራት በሰጡት ምላሽ÷ በዕጣ እና በጨረታ የመኖሪያ እና የንግድ ቤት የወጣላቸውና ውል የፈጸሙ ሰዎች ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ሁለት ጊዜ የጥሪ ማስታወቂያ መውጣቱን አስታውሰዋል።

ይህን ተከትሎም በተለያዩ ሳይቶች ሰዎች መግባት መጀመራቸውን እና ውል ተፈጽሞባቸው ክፍት የሆኑ ቤቶች መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡

“ሰዎች ባልገቡባቸው የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ሕገ-ወጥ ድርጊት እየተፈጸመ ነው” የሚለው መረጃ እንደደረሳቸው ገልጸው፤ ይህ የሚሆነው ግን ሰዎቹ ውል ፈጽመው ባልገቡባቸው ስለሆነ ችግሩን ለማስቀረት የግድ ሰዎቹ ወደ ቤቶቹ መግባት አለባቸው ብለዋል፡፡

ከመሠረተ-ልማት አለመሟት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን አንስተው፤ በተለያዩ ሳይቶች መሠረተ-ልማት ተሟልቶ ነዋሪዎች መግባታቸውን እና ባልተሟላላቸው ደግሞ ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔዎችን እየተሰጠ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በዚሁ መሠረት የውኃ፣ ኤሌክትሪክ፣ መንገድ እና ሌሎች መሠረተ-ልማቶች እንዲሟሉ እየሠራን ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ÷ ለአብነትም በቦሌ አራብሳ ሳይት ዘላቂ የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ለማቅረብ ‘ትሪትመንት ፕላንት’ እየተሠራ ነው፤ በሁለት ወራትም ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡

እንዲሁም በሃያት ጨፌ አካባቢ 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የመሠረተ-ልማት ማሟላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እስከዚያው ድረስም ለችግሮቹ ጊዜያው መፍትሔ እየተሰጠ መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡

ሁሉንም ጥያቄዎች በአንድ ጀምበር መቅረፍ አይቻልም፤ የሥራው ባሕሪ በራሱ ጊዜ ይፈልጋል እኛም በዚህ አግባብ እየሠራን መሆናችንን በመገንዘብ ውል የፈጸሙ ዕድለኞች እስከ ሕዳር 30 ቀን 2017 ድረስ መግባት አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ሰዎች የማይገቡ ከሆነ ግን የቤቶቹን ቁጥርና ሌሎች አስፈላጊ ተያያዥ ሁኔታዎች በማጣራትና በመለየት በየደረጃው ለሚገኙ አካላት ውሳኔ እንዲሰጥበት እናቀርባለን ነው ያሉት፡፡

በተለያዩ ዓመታት በ20/80 14 ዙር፣ በ40/60 3 ዙር እንዲሁም በጨረታ 17 ዙር በዕጣና ጨረታ የማስተላለፍ ሥራ መከናወኑን አስታውሰው÷ ከእነዚህ መካከል ውል ፈጽመው ወደ ቤታቸው የገቡ እና ለመግባት ውል እየፈጸሙ ያሉ እንዲሁም ውል ፈጽመው ያልገቡ እንዳሉ አብራርተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው