አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ ገንቢ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የአውሮፓ ህብረት ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገርን ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሚኒስትሩ የአውሮፓ ሕብረት ኢትዮጵያ በማኀበረ-ኢኮኖሚ መስኮች ለማሻሻል ለምታደርገው ጥረት ቁልፍ አጋር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደምትሰራና በተለይም በልማት ትብብር፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ግንኙነቱን ለማስፋት ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለአምባሳደሯ በቀጣናው ስላለው ወቅታዊ የሰላም እና ፀጥታ ሁኔታ ገለጻ አድርገዋል።
አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገር በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በቀጣናው ካላት ጉልህ ስትራቴጂካዊ ሚና አኳያ ሕብረቱ ከሀገሪቱ ጋር ላለው ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ከ180 በላይ የአውሮፓ ኩባንያዎች እንደሚገኙ በመጥቀስ ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኩባንያዎቹ የበለጠ ዕድል የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በማድረግ ገንቢ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አምባሳደሯ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።