አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በየመን የሚንቀሳቀሰው የሁቲ አማጺ ቡድን በሁለት የአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ በድሮን እና በሚሳዔል የታገዘ ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ።
ቡድኑ ንብረትነታቸው የአሜሪካ የሆኑ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ የሆነችውን መርከብ ጨምሮ በሁለት መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።
የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት ፔንታጎን በበኩሉ ወደ የመን ባህር ዳርቻ በማቅናት ላይ የነበሩ የጦር መርከቦች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አረጋግጧል።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሜጀር ጀነራል ፓትሪክ ራይደር የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ የተሰነዘረው ጥቃት ምንም አይነት ጉዳት ሳያደርስ ማክሸፍ መቻሉን ተናግረዋል።
ቡድኑ ጥቃቱን የፈጸመው በስምንት ድሮኖች፣ አምስት ባላስቲክ ሚሳኤሎች እንዲሁም ሶስት ክሩዝ ሚሳኤሎች እንደሆነም ቃል አቀባዩ ገልጸው፤ በጥቃቱ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ጠቁመዋል።
የሁቲ አማጺ ቡድን ቃል አቀባይ ያህያ ሳርኣ በበኩሉ ስምንት ሰዓት በፈጀው የአሜሪካ የጦር መርከቦችን እንዲሁም ጸረ ሚሳኤሎችን የማውደም ኦፕሬሽን የሚፈለገውን ኢላማ መምታት መቻሉን እንደተናገረ የዘገበው አልጀዚራ ነው።
ዋና ከተማዋን ሰነዓ ጨምሮ በርካታ የየመን አካባቢዎችን የተቆጣጠረው ቡድኑ፤ በቀይ ባህር እና ኤደን ባህረ ሰላጤ በሚንቀሳቀሱ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው መርከቦች ላይ ከፈረንጆቹ 2023 ህዳር ወር ጀምሮ ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል፡፡