አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሚራ ይማም ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ እስከሚመስል ሴቶች እምብዛም በማይሰማሩበት የሀገር አቋራጭ የከባድ መኪና አሽከርካሪነት የስራ መስክ የተሰማራች የሁለት ልጆች እናት ናት::
በአስራዎቹ እድሜ በነበረችበት ወቅት በአንድ ድርጅት የመንገድ ሥራ ማሽኖች ተቆጣጣሪ በመሆን ሥራዋን አሃዱ ብላ የጀመረችው ሰሚራ፤ በምትሰራበት ድርጅት በምታሳየው የስራ ተነሳሽነትና እልህ ከአሰሪዎቿ አድናቆት ይሰጣት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
በዚህ መነሳሳትም የ21ኛ ዓመት ልደቷ በቀድሞ 5ኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ በመያዝ የከባድ መኪና አሽከርካሪነት ስራ ጀምራለች።
“አባቴ ገና የአንድ ዓመት ህፃን እያለሁ በመሞቱ እናቴ እንደአባትም እንደእናትም ፈተና ተጋፍጣ አሳድጋኛለች” የምትለው ሰሚራ፤ ብርታትን እና ጥንካሬን ከእናቷ መማሯን ትናገራለች።
ከዓመታት በፊት ሀገሯ በችግር ቀኗ ስትፈልጋት አለሁልሽ ብላ በሙያዋ ለማገልገል በጦር ሜዳ ተሰልፋለች።
ለአራት ዓመታት ስታገለግል በቆየችበት ጊዜም የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ትራንስፖርት መምሪያ ላስመዘገብሽው ውጤታማ አፈጻጸም ይህ ይገባሻል በማለት እውቅና ችሯታል።
በአንድ ወቅት የሦስት ዓመት ልጇን በጭኖቿ ላይ አስተኝታ በእጆቿ ደግሞ መሪዋን ጨብጣ አስቸጋሪ በሚባል መንገድ በጦርነት ቀጣና ውስጥ ሆና ለማሽከርከር የተገደደችበት ጊዜ ከፈተናዎቿ አንዱ እንደነበር ታስታውሳለች።
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች አለፍ ሲልም ጅቡቲ ድረስ ተሳቢ መኪና እያሽከረከረች በመስራት ልጆቿን የምታሳድገው ሰሚራ፤ ለብዙዎች አስቸጋሪ የሚመስለውን የሀገር አቋራጭ የከባድ መኪና አሽከርካሪነት ሀላፊነቷን በብቃት ትወጣለች።
በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚያገኟት ሰዎች ለሚሰጧት አድናቆት እና ማበረታቻ በተለይም ደግሞ በስራ ላይ ለሚገጥማት እክል የሙያ አጋሮቿ ለሚያደርጉላት ድጋፍና እንክብካቤ ምስጋናዋን ትገልጻለች።
የሾፌርነት ሙያ እንደተሸከመው ሀላፊነት ክብር አልተሰጠውም ምትለው ሰሚራ፤ ሙያው በሁሉም ዘንድ ክብር አግኝቶ ማየት ምኞቷ እንደሆነም ትናገራለች።
“ጥበቃው ሌባ ናት ብሎ በዱላ አሯሯጠኝ…” የከባድ መኪና አሽከርካሪዋ እንስት ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር የነበራትን ቆይታ በዚህ ሊንክ ይመልከቱ https://www.youtube.com/watch?v=xw0pMzeiGAA
በበፀሎት መንገሻ