የሀገር ውስጥ ዜና

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉን ማዘመን እንደሚገባ ተመላከተ

By ዮሐንስ ደርበው

November 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የያዘችውን ዘርፈ-ብዙ ዕድገት የሚመጥን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመገንባት ዘርፉን ማዘመን እንደሚገባ ተመላከተ፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የ2017 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም የሴክተር ግምገማ በሐረር  ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡

በዚሁ ወቅት ዘርፉ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የያዘችውን ዕድገት የሚመጥን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመገንባት ዘርፉን ማዘመን እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት ዘርፉን በማዘመን የሀገሪቱን ገቢና ወጪ ዕቃዎች በፍጥነት ለማጓጓዝ ጥረት መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ለመንገድ ልማት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው÷ 1 ቢሊየን ብር ለመንገድ ልማት  ሥራ መመደቡን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ የቱሪዝም ፍሰቱን ለማሳለጥም የአየር ትራንስፖርት አማራጭን ለማስፋት ጥረት መጀመሩን አመላክተዋል።

ሚኒስቴሩም ሐረር ከተማ የዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያ ባለቤት እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢዮናዳብ አንዱዓለም