አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በዑጋንዳ ካምፓላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊቷ ወ/ሮ ብሔር ክፍሌ ቦሪ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ የ31 ሺህ 425 የአሜሪካ ዶላር ቦንድ ግዢ ፈጽመዋል፡፡
ወ/ሮ ብሔር በዑጋንዳ ኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገኝተው የቦንድ ግዢውን መፈጸማቸውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
የቦንዱን ሠነድም ግለሰቧ ከአምባሳደር እጸገነት በዛብህ ይመኑ እጅ ተረክበዋል፡፡
በዚሁ ወቅት አምባሳደሯ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሀገራችን ኩራት ነው፤ ወ/ሮ ብሔርና ቤተሰቦቻቸውም ግድባችን ከዳር እንዲደርስ በተደጋጋሚ እያደረጉት ላለው ድጋፍ እናመሠግናለን ብለዋል፡፡
ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ወ/ሮ ብሔር በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሀገራችን ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ሀገራዊ ፕሮጀክት ስለሆነ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡