አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 4ኛው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በሶማሌላንድ እየተካሄደ ይገኛል።
ምርጫው ለሶማሌላንዳውያን ወሳኝ መሆኑን መራጮች የገለጹ ሲሆን፥ ለሰላም፣ ልማትና አንድነታቸው ምርጫው ወሳኝ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ይህ ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች ለሁለት ዓመት መዘግየቱን የሚያነሱት መራጮቹ፥ ምርጫው በመዘግየቱ ምክንያት ያጋጠሙ ችግሮችን እንደሚፈታላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል።
በዛሬው እለት እየተደረገ ባለው ምርጫ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የሚመሩት ፒስ ዩኒቲ ኤንድ ዴቭሎፕመንት ፓርቲ፣ አብዲራሃማን ሞሃመድ አብዱላሂ የሚወክሉት ሶማሌላንድ ናሽናል ፓርቲ እና በፋይሳል አሊ ዋራቤ የሚመራው ጀስቲስ ኤንድ ዌልፌር ፓርቲ እየተፎካከሩ ነው።
በሥድስት ክልል በ2 ሺህ 648 ምርጫ ጣቢያ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ መራጮች ድምፃቸውን እየሰጡ ነው።
በታሪኩ ለገሰ ከሃርጌሳ