Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ኢኢጂ የተሰኘ የሚጥል ህመም መመርመሪያ ማሽን ለሆስፒታሎች አስረከቡ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ኤሌክትሮኢንሴፋሎግራፊ (ኢኢጂ) የተሰኘ የሚጥል ህመም መመርመሪያ ማሽን ለሆስፒታሎች አስረክበዋል፡፡

ማሽኑ የሚጥል ህመምን ጨምሮ ለአንጎል ህክምና መመርመሪያነት የሚያገለግል ሲሆን፤ በቴክኖሎጂና በካሜራ የታገዘ ምርመራ በማድረግ ተገቢ ህክምና ለማስገኘት ከፍተኛ አቅም ያለው መሆኑ ተነግሯል።

ማሽኖቹ ለጥቁር አንበሳ ስፔሸላይዝድ ሆስፒታል፣ ለጦር ሀይሎች ሆስፒታል፣ ለአዳማ ሆስፒታል፣ ለሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል፣ ለጂግጂጋ ሪፈራል ሆስፒታል፣ ለጎንደር አጠቃላይ ሆስፒታል እና ለአይደር ሆስፒታል ነው የተበረከቱት፡፡

በዚህም የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከሚሰራባቸው የትኩረት አቅጣጫዎች ውስጥ አንዱ በሆነው የአእምሮ ጤናና እና ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫና የተሻለ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ የማጠናከር ስራ አንዱ አካል እንደሆነ ተገልጿል።

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በአዕምሮ ህመምና ህክምና ዙሪያ የህክምና መሳሪያም ሆነ የባለሙያ እጥረት መኖሩን አስታውሰዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በዚህ ዘርፍ የሚያደርገው ተከታታይ ድጋፍ አድናቆት የሚቸረው መሆኑንም አንስተዋል።

የህክምና መሳሪያው ከዚህ በፊት በጥቂት ሆስፒታሎች የሚሰጠውን በሰዓት የተገደበ አገልግሎት የሚቀርፍና ታካሚው ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ አገልግሎቱን እንዲያገኝ የሚያስችል ሲሆን ለ24 ሰዓት ግልጋሎት የሚሰጥ እንደሆነም ታምኖበታል።

ድጋፉን ያገኙ የህክምና ተቋማት ባለሙያዎች ቀደም ብለው በማሽኑ አሰራር ዙሪያ በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት አስተባባሪነት ስልጠና መውሰዳቸውም ተጠቁሟል፡፡

የተለገሰው ማሽን የሚጥል ህመም፣ የአንጎል እና ተያያዥ ህክምናን በጥሩ አቅምና አጭር ሰዓት ምርመራን ከማድረግ በተጨማሪ አገልግሎቱን ፍለጋ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን ጉዞና እንግልት እንደሚቀርፍ ገልጸዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በነርቭና የአንጎል ህክምና ዙሪያ ያለውን ክፍተት በመረዳት ማሽኖቹን በውጭ ሀገር ከሚገኙ ለጋሾች ጋር በትብብር አስመጥቷቸዋል።

ጽህፈት ቤቱ ከዚህ ቀደም የኤሌክትሮኢንሴፋሎግራፊ መመርመሪያ መሳሪያ ለአማኑኤል የአእምሮ ስፔሸላይዝድ ሆስፒታል በስጦታ ማበርከቱ ይታወሳል።

በፍሬህይዎት ሰፊው

Exit mobile version