የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንሰራለን – ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

By amele Demisew

November 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ቻይና መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንሰራለን ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼይ ሀይን ጋር ባደረጉት ውይይት፤ የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በሁኔታዎች የማይለወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት መድረሱን አስታውሰዋል።

ይህን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰራ ገልጸው፤ የኢትዮ-ቻይናን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በአፍሪካ ቻይና የትብብር መድረክ (ፎካክ) ማዕቀፍ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለመተግበር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያም ገለጻ ያደረጉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በሁለትዮሽ ብቻ ሳይሆን በባለብዙ ወገን ግንኙነት በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና ፀጥታ ዙሪያ በጋራ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ቼይ ሀይን በበኩላቸው በፎካክ ጉባዔ ላይ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች መግባባት ላይ የደረሱባቸውን የኢኮኖሚ፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የብሪታኒያ አምባሳደር ዳረን ዊልችን ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በቀጣናው ሠላም እና ፀጥታ፣ በሱዳን እና ሶማሊያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ መክረዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ከቀጣናው አልፎ ለዓለምዓቀፉ ማህበረሰብ አሳሳቢ ጉዳይ እንደመሆኑ ለመፍትሄውም የጋራ ምክክር እንደሚያሻው አምባሳደር ዊልች በውይይቱ ወቅት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ እየተገበረች ለሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ብሪታኒያ እያደረገች ላለው ድጋፍ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ምስጋና አቅርበዋል።